6. የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ሊቀበልህ በመምጣት ላይ ነው፤ አራት መቶ ሰዎችም አብረውት አሉ” አሉት።
7. ያዕቆብም በታላቅ ፍርሀትና ጭንቀት ተውጦ፣ አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁለት ቦታ ከፈላቸው፤ በጎቹን ፍየሎቹን ከብቶቹንና ግመሎቹንም ሁለት ቦታ ከፈላቸው፣
8. “ዔሳው መጥቶ በአንደኛው ላይ አደጋ ቢጥል፣ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ አስቦ ነበር።
9. ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) ሆይ፤ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤