13. ስለዚህ ሙሴ በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) በዚያን ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግሥቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ።
14. እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም።
15. ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ፣ ጠርገው በሉ። በግብፅ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።