10. ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ይሁን ነገር ግን ተንኰል አስባችኋል።
11. አይሆንም ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።
12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብፅ አገር ላይ ዘርጋ” አለው።
13. ስለዚህ ሙሴ በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) በዚያን ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግሥቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ።
14. እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም።