ዘዳግም 1:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።”

9. “እኔም በዚያን ጊዜ እንዲህ አልኋችሁ፤ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤

10. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቊጥራችሁን ጨምሮአል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል።

11. አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሺህ ጊዜ ያብዛችሁ፤ በሰጠውም ተስፋ መሠረት ይባርካችሁ

12. ይሁን እንጂ ችግራችሁን፣ ሸክማችሁንና ክርክራችሁን ሁሉ ብቻዬን እንዴት አድርጌ መሸከም እችላለሁ?

13. ጥበበኞችን፣ አስተዋዮችንና የተከበሩ ሰዎችን ከየነገዳችሁ ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።”

14. እናንተም፣ “ይደረግ ዘንድ ያቀረብኸው ሐሳብ መልካም ነው” ብላችሁ መለሳችሁልኝ።

15. ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች ጥበበኞችንና የተከበሩትን ሰዎች ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ አምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው።

16. በዚያን ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በትክክል ፍረዱ።

17. በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።”

ዘዳግም 1