ዘካርያስ 13:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “በዚያ ቀን የዳዊትን ቤትና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከኀጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።

2. “በዚያ ቀን የጣዖታትን ስም ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም አይታሰቡም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። “ነቢያትንና ርኵስ መንፈስን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።

3. ማንም ትንቢት ቢናገር ወላጅ አባትና እናቱ፣ ‘በእግዚአብሔር ስም ሐሰት ተናግረሃልና ሞት ይገባሃል’ ይሉታል። ትንቢት ሲናገርም የገዛ ወላጆቹ ይወጉታል።

4. “በዚያን ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ስለሚናገረው የትንቢት ራእይ ያፍራል፤ ለማታለልም የነቢያትን ጠጒራም ልብስ አይለብስም።

5. እርሱም፣ ‘እኔ ገበሬ እንጂ ነቢይ አይደለሁም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ኑሮዬ የተመሠረተውም በዕርሻ ላይ ነው’ ይላል።

6. አንድ ሰው፣ ‘ይህ በሰውነትህ ላይ ያለው ቊስል ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቀው፣ ‘በባልንጀሮቼ ቤት ሳለሁ የቈሰልሁት ነው’ ይላል።

7. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤“ሰይፍ ሆይ፤ በእረኛዬ፣በቅርብ ወዳጄ ላይ ንቃ!እረኛውን ምታ፤በጎቹ ይበተናሉ፤እኔም ክንዴን ወደ ታናናሾቹ አዞራለሁ።

ዘካርያስ 13