8. ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም፤
9. በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”
10. ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤
11. “ወደ ሰፈር ግቡ፤ ለሕዝቡም፣ ‘ስንቃችሁን አዘጋጁ፤ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ትወርሳላችሁ’ በሏቸው።”
12. ኢያሱ የሮቤልን ነገድ፣ የጋድን ነገድና የምናሴን ነገድ እኩሌታ እንዲህ አላቸው፤