1. “እናንት ጽድቅን የምትከታተሉ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉ ስሙኝ፤ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጒድጓድ ተመልከቱ።
2. ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤በጠራሁት ጊዜ አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ባረክሁት፤ አበዛሁትም።
3. እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤ተድላና ደስታ፣ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በእርሷ ይገኛሉ።