ሕዝቅኤል 46:12-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ገዡ በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ በምሥራቅ ትይዩ የሆነው በር ይከፈትለት፤ በሰንበት ቀን እንደሚያደርገው ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕቱንም ሆነ የኅብረት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይወጣል፤ በሩም ይዘጋል።

13. “ ‘በየቀኑ እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ ይህንንም በየማለዳው ታቀርበዋለህ።

14. ከዚህም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት መለወሻም የሚሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት አድርገህ በየማለዳው የእህል ቍርባን አቅርብ፤ ይህን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ማቅረብም የዘላለም ሥርዐት ነው።

15. ስለዚህ ዘወትር ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በየማለዳው የበግ ጠቦት፣ የእህል ቍርባንና ዘይት ይቅረብ።

ሕዝቅኤል 46