ሕዝቅኤል 40:17-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ እዚያም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ክፍሎችና ድንጋይ የተነጠፈበት መመላለሻ አየሁ፤ በመመላለሻውም ዙሪያ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።

18. የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋር ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።

19. ከዚያም ከታችኛው መግቢያ በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት አንድ መቶ ክንድ ነበር።

20. ከዚያም በሰሜን ትይዩ ያለውን፣ ወደ ውጩ አደባባይ የሚያመራውን በር ርዝመትና ወርድ ለካ።

21. እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

22. መስኮቶቹ፣ መተላለፊያ በረንዳዎቹና የዘንባባ ዛፍ ቅርጾቹ ልካቸው በምሥራቁ በር ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ወደዚያ የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያ በረንዳዎቹም ከእነርሱ ጋር ትይዩ ነበር።

ሕዝቅኤል 40