14. በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንት የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ።
15. ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም።
16. ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤
17. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን፣መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ጒልማሶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ።
18. በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ፣መንፈሴን አፈሳለሁ፤እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።