7. እርሷም ሄዳ ይህንኑ ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው። እርሱም፣ “ሄደሽ ዘይቱን በመሸጥ ዕዳሽን ክፈይ፤ የተረፈውም ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።
8. አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሄደ። በዚያም አንዲት ሀብታም ሴት ነበረች፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር ምግብ ለመብላት ወደ ቤቷ ይገባ ነበር።
9. ሴቲቱም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ “ይህ አዘውትሮ በደጃችን የሚያልፍ ሰው፣ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ዐውቃለሁ፤
10. ስለዚህ በሰገነቱ ላይ አንዲት ትንሽ ክፍል ቤት ሠርተን ዐልጋና ጠረጴዛ፣ ወንበርና ፋኖስ እናስገባለን፤ ከዚያም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች።”