24. ከዚያ እናንተ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶ በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።”ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “ያልኸው መልካም ነው” አሉ።
25. ኤልያስም ለበኣል ነቢያት፣ “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ፤ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ግን እሳት አታንድዱበት” አላቸው።
26. ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የበኣልን ስም ጠሩ፤ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር።
27. እኩለ ቀንም ላይ ኤልያስ፣ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ አምላክ አይደለም እንዴ! ምናልባት በሐሳብ ተውጦ ወይም ሥራ በዝቶበት፣ አልያም በጒዞ ላይ ይሆናል፤ ተኝቶም ከሆነ ቀስቅሱት” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር።